የኢትዮጵያውያን  ፡ ሀገራዊ  ፡ ሥልጡንሕዝባዊ  ፡ አንድነት  ። Ethiopians' Citizen Democratic Union | Union Citoyenne Démocratique des Éthiopiens የመርበቢያ ፡ አድራሻ ፤ www.slttunhzb.net የእ-ጦማር ፡ አድራሻ ፤ sh1@ttomar.net ገ_ዐዓ_20150116_ዐማርኛ ለ2015 ፡ ዓ.ም. ፡ የመልካም ፡ ምኞት ፡ መግለጫ ። የኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ የ2015 ፡ ዓ.ም. ፡ መልካም ፡ ምኞት ፡ መልእክት ፡ ለኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፦ « አንዲት ፡ ኢትዮጵያ ፡ ወይም ፡ ሞት ! »  _______ ለንደን፥ መስከረም ፡ 16 ፡ ቀን ፡ 2015 ፡ ዓ.ም.። የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ሆይ! የዘመናት ፡ ጌታ ፥ ቸር ፡ አምላክ ፡ እንኳን ፡ ከዘመን ፡ እዘመን ፡ በደኅና ፡ አሸጋገረኽ ፡ እያለ ፥ ውጥን ፡ አካልኽ ፥ የኢትዮጵያውያን ፡ ሀገራዊ ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ አንድነት ፡ ( ኢ.ሀ.ሥ.አ. ) ፡ መልካም ፡ ምኞቱን ፡ በፍጹም ፡ ትሕትና፡ያቀርብልኻል ። መስከረም ፡ 16 ፡ ቀን ፡ 1945 ፡ ዓ.ም. ፥ አስቀድሞ ፡ ለ60 ፡ ዓመታት ፡ "ኤርትራ" ፡ በሚል ፡ ስም ፥ በቅኝ ፡ ገዢዎች ፡ ቀንበር ፡ ሥር ፡ ወድቀው ፡ የነበሩት ፡ የባሕር ፡ ምድር ፡ እና ፡ የደንከል ፡ ጥንታውያን ፡ የኢትዮጵያ ፡ ክፍሎች ፥ በነዋሪዎቻቸው ፡ ትግል ፡ እና ፡ በኢትዮጵያ ፡ ንጉሠ ፡ ነገሥታዊ ፡ መንግሥት ፡ ጥያቄ ፡ መሠረት ፥ በተባበሩት ፡ መንግሥታት ፡ ድርጅት ፡ ውሳኔ ፡ ዳግመኛ ፡ ከእናት ፡ ሀገራቸው ፡ ኢትዮጵያ ፡ ጋራ ፡ በድበላ ፡ ( በfederation ) ፡ ሥርዐት ፡ የተቀላቀሉበት ፡ ዕለት ፡ ነው ። ዘንድሮ ፡ 70ኛ ፡ ዓመቱን ፡ እናስባለን ። ዳሩ ፡ ግን ፥ « አንዲት ፡ ኢትዮጵያ ፡ ወይም ፡ ሞት ! » ፡ በሚል ፡ መሪ ፡ ቃል ፡ የታገሉ ፡ ነዋሪዎቻቸውም ፡ ኾኑ ፡ የኢትዮጵያ ፡ ንጉሠ ፡ ነገሥታዊ ፡ መንግሥት ፥ ለተባበሩት ፡ መንግሥታት ፡ ድርጅት ፡ ያመለከቱት ፡ ለመዋሐድ ፡ እንጂ ፡ ለመዳበል ፡ አልነበረም ። በተባበሩት ፡ መንግሥታት ፡ ድርጅት ፡ የተጫነባቸው ፡ ይህ ፡ ደባል ፡ ዐዳር ፡ ለዐሥር ፡ ዓመታት ፡ በገቢር ፡ ከታየ ፡ በዃላ ፥ ከጥቅሙ ፡ ጕዳቱ ፡ ማመዘኑን ፡ ሲያረጋግጡ ፥ የክፍለ ፡ ሀገሪቱ ፡ነዋሪዎች ፥ በተወካዮቻቸው ፡ አማካይነት ፡ በምክር ፡ ቤት ፡ መክረውና ፡ ዘክረው ፥ በሙሉ ፡ ድምፅ ፡ ውሳኔ ፡ ድበላውን ፡ ገፍተው ፥ ከኢትዮጵያ ፡ ጋራ ፡ ፈጽሞ ፡ የመዋሐድ ፡ ውዴታቸውን ፡ ለኢትዮጵያ ፡ ንጉሠ ፡ ነገሥታዊ ፡ መንግሥት ፡ አስተላለፉ ። የኢትዮጵያ ፡ ንጉሠ ፡ ነገሥታዊ ፡ መንግሥትም ፥ ነዋሪዎቹ ፡ ያስተላለፉለትን ፡ ውዴታ ፡ አክብሮ ፥ የኢትዮጵያን ፡ ክዋኔ ፡ በማሻሻል ፥ ኅዳር ፡ 5 ፡ ቀን ፡ 1955 ፡ ዓ.ም. ፡ ክፍለ ፡ ሀገር ፡ ኤርትራን ፡ 14ኛ ፡ ጠቅላይ ፡ ግዛቱ ፡ አድርጎ ፡ በእግዚእናው ፡ አዋሐዳት ። ዘንድሮ ፥ ኤርትራ ፡ ከእናት ፡ ሀገሯ ፡ ከኢትዮጵያ ፡ የተዋሐደችበትን ፡ 60ኛ ፡ ዓመት ፡ እናስባለን ። የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ሆይ ! ካ11 ፡ ዓመታት ፡ በዃላ ፡ ግን፥ በ1966 ፡ ዓ.ም. ፥ ከሺሕ ፡ ዓመታት ፡ በፊት ፡ ራስኽ ፡ በእግዚእናኽ ፡ የከወንከው ፡ ንጉሠ ፡ ነገሥታዊው ፡ መንግሥትኽ ፡ ከውጭ ፡ በተመራ፟ ፡ ዐመፅ ፡ ተደርምሶ ፥ እንሆ ፥ እስከ ፡ ዛሬ ፡ ድረስ ፡ ለ49 ፡ ዓመታት ፡ በተፈራረቁብኽ ፡ የውንብድና ፡ አገዛዞች ፡ ሥር ፡ ወድቀኽ ፥ ክፍለ ፡ ሀገር ፡ ኤርትራም ፡ ዳግም ፡ ተገንጥላ ፥ ሀገር ፡ ኢትዮጵያም ፡ በ"አፓርትሀይድ" ፡ የድበላ ፡ ወጥመድ ፡ ውስጥ ፡ተገርኝታ ፥ የመበ፟ታተንና ፡ የጥፋት ፡ አደጋዎች ፡ ተደቅነውብኻል ። የኢትዮጵያውያን ፡ ሀገራዊ ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ አንድነት ፡ ( ኢ.ሀ.ሥ.አ. ) ፥ መፍትሔ ፡ ይኾንልኻል ፡ ብሎ ፡ባመነው ፡ መሠረት ፥ የሥልጡንሕዝብናኽን ፡ ርትዕ ፡ ተመርኵዞ ፥ ሕዝባዊ ፡ አንድነታዊ ፡ አካልኽን ፡ መልሶ ፡ ለማቋቋምና ፥ በአንድነት ፡ ሥልጣንኽ ፡ አማካይነት ፡ ሀገራዊ ፡ እግዚእናኽን ፡ ለማስከበር ፡ ገና ፡ በ1967 ፡ ዓ.ም. ፡ ትግሉን ፡ ተቀላቅሏል ። የዘመኑ ፡ መርዘም ፡ የትግሉን ፡ አስቸጋሪነት ፣ የባለጋራዎቻችንንም ፡ ኀያልነት ፡ የሚያመለክተውን ፡ ያኽል ፥ ወደ ፡ ፊት ፥ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ አንድነታዊ ፡ አካልኽ ፡ ሞልቶ ፡ በሚገኝበት ፡ ሰዓት ፡ ያንኑ ፡ ያኽል ፡ ፍጡን ፡ ፈውስ ፡ እንደምታገኝበት ፡ ያረጋግጣል ። ይህ ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ አንድነታዊ ፡ አካልኽ ፡ የሚገሠግሥበት ፡ መርሕ ፡ እና ፡ ስልት ፡ አስቀድሞ ፡ በኤርትራ ፡ የአንድነት ፡ ትግል ፡ ዘመን ፡ ( 1933 - 1945 ፡ ዓ.ም. ) ፥ በወቅቱ ፡ የኢትዮጵያ ፡ አገናኝ ፡ መኰንን ፡ በነበሩት ፡ በሊ. ፡ ዤኔራል ፡ ነጋ ፡ ኀይለ ፡ ሥላሴ ፡ አሳሳቢነት ፥ የክፍለ ፡ ሀገር ፡ ኤርትራ ፡ ሕዝብ ፡ ከኢትዮጵያ ፡ ጋራ ፡ የመዋሐድ ፡ ትግሉን ፡ በድል ፡ የተወጣበት ፡ ስያሳዊ ፡ መርሕ ፡ እና ፡ ስልት ፡ ስለ ፡ ኾነ ፥ ፍቱን ፡ ፈውስነቱንም ፡ በታሪክ ፡ ማስመስከሩን ፡ እናስታውሳለን ። ሊ. ፡ ዤኔራል ፡ ነጋ ፡ ኀይለ ፡ ሥላሴ ፥ በ1966-67 ፡ ዓ.ም. ፥ የወቷደራዊ ፡ ደርግን ፡ የውንብድና ፡ አገዛዝ ፡ ከተቃወሙ ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ሕጋውያን ፡ ተወካዮች ፡ በተደጋጋሚ ፡ በተላከላቸው ፡ ውክልና ፡ እና ፡ ዐደራ ፡ መሠረት ፥ በስደት ፡ ዓለም ፡ ከጥቂት ፡ ሀገራውያን ፡ ኢትዮጵያውያን ፡ ጋራ ፡ ኢ.ሀ.ሥ.አ.ን ፡ በሥልጡንሕዝባዊ ፡ መሠረት ፡ ላይ ፡ በሐምሌ ፡ ወር ፡ 1967 ፡ ዓ.ም. ፡ ለንደን ፡ ላይ ፡ አቋቁመው ፥ ትግሉን ፡ በዚሁ ፡ ስልት ፡ መርተዋል ። እንሆ ፡ ዛሬ ፥ የኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ ጊዜያዊ ፡ ፈጻሚ ፡ ምክር ፥ ይህኑ ፡ ሥራ ፡ በሰፊው ፡ በማረማመድ ፥ መላ፟ውን ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ለማስተባበር ፡ ተነሥቷል ። የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ሆይ ! ሀገራዊ ፡ የአንድነት ፡ ሥልጣንኽ ፡ ከቀበሌ ፡ አንሥቶ ፡ እስከ ፡ ወረዳ ፣ እስከ ፡ አውራጃ ፣ እስከ ፡ ክፍለ ፡ ሀገር ፡ እና ፡ እስከ ፡ መላ፟ ፡ ኢትዮጵያ ፡ የሚዋቀርበትን ፡ ትውፊታዊ ፡ ስልት ፡ በማዘመን ፥ ሀገራዊው ፡ የሥልጣን ፡ ተዋረድ ፡ የሚ፟በ፟ጅ፟በ፟ትንና ፡ ዐዲሱን ፡ ክዋኔኽን ፡ ( ወይም ፡ ዐዲሱን ፡ ሕገ ፡ መንግሥትኽን ) ፡ በሕጋውያን ፡ ተወካዮችኽ ፡ አርቅቀኽ ፡ የምታጸድቅበትን ፦ « ሥልጡንሕዝባዊ ፡ የመሸጋገሪያ ፡ መንግሥት ፡ ሀገራዊ ፡ ቅያስ »፥ እንሆ ፥ የኢ.ሀ.ሥ.አ.፡ ጊዜያዊ ፡ ፈጻሚ ፡ ምክር ፡ ሲያሰናዳ ፡ ከርሞ ፥ የመጨረሻ ፡ ረቂቁን ፡ በዛሬው ፡ ዕለት ፥ መስከረም ፡ 16 ፡ ቀን ፡ 2015 ፡ ዓ.ም. ፡ ያጸደቀው ፡ መኾኑን ፡ በታላቅ ፡ ደስታ ፡ ያበሥርልኻል ። ሰነዱንና ፡ ዐብረውት ፡ የሚወጡትን ፡ ተያያዥ ፡ ሰነዶች ፡ በቅርቡ ፡ በመርበቢያችን ፡ በ፦ www.slttunhzb.net አማካይነት ፡ ላስተያየትኽ ፡ የምናደርስልኽ ፡ መኾናችንን ፡ በታላቅ ፡ አክብሮት ፡ እናስታውቃለን ። የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ሆይ ! በሥልጡንሕዝባዊ ፡ አንድነታዊ ፡ አካልኽ ፡ ሙሉ ፡ ችሎት ፡ የማይፈ፟ታ፟ ፡ አንድም ፡ ችግር ፡ የለብኽምና ፥ ዓመቱ ፡ ይህን ፡ ሀገራዊ ፡ ክሂልኽን ፡ የምታሞላበት ፣ ሀገራዊ ፡ እግዚእናኽን ፡ የምታስከብርበት ፡እና ፡ ሥልጡንሕዝባዊት ፡ ኢትዮጵያን ፡ ባዲስ ፡ ክዋኔ ፡ ( ባዲስ ፡ ሕገ ፡ መንግሥት ) ፡ ዳግም ፡ የምትከውንበት ፡ ዓመት ፡ እንዲኾንልኽ ፡ ኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ ከልብ ፡ ይመኝልኻል ፤ በተጋድሎኽም ፡ ዅሉ ፡ ከጐንኽ ፡ አይለ፟ይ፟ም ፨ ትሑት፡አገልጋይኽ፦ ኢ.ሀ.ሥ.አ.